ከትግራይ ክልል ተወላጅ ወጣቶች ጋር በተለያዩ የሀገሪቱ ከፍሎች ውይይት ሊካሄድ ነው

ከትግራይ ክልል ተወላጅ ወጣቶች ጋር ውይይት ሊካሄድ  መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ ገለፀ።

ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ስራ ሲሰራ ቆይቶ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሰተዳደር ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር በመሆን የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መደበኛ ስራዎች ወደ መምራትና ወደ ቀድሞው ሁኔታ የመመለስ ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡

በመሆኑም በቅርቡ የወጣቶች ሊግ ስራ አስፈጻሚ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ህግ የማስከበር ስራ ለወጣቶች ያለው ፋይዳ፣ አሁናዊ የክልሉ ሁኔታና ከወጣቶች በሚጠበቁ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚኖሩ የክልሉ ተወላጅ ወጣቶች ጋር ውይይት ያደርጋል ተብሏል፡፡

በዚሁ መሰረት በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን በቀጣይ በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ውይይቱ እንደሚቀጥልና የብልጽግና ወጣቶች ሊግ መዋቅርን በአዲስ መልክ የማደራጀት ስራ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን እንደሚያከናውን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡