ከትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርቡ ወቀሳዎች በመረጃ ያልተደገፉ ናቸው – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ

 

የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የህግ ማስከበር እርምጃ እና ከእርምጃው መጠናቀቅ በኋላ በክልሉ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርቡ ወቀሳዎች በመረጃ ያልተደገፉ መሆናቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ ዋና ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ አስታወቁ።

አቶ ለማ ተሰማ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ ቦርዱ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እና አጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች በሁለት ዙር ተዘዋውሮ ጉብኝት አድርጓል፡፡

እንደ ሰብሳቢው ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርቡ ወቀሳዎች በመረጃ ያልተደገፉ ናቸው።

ለእነዚህ አካላት ሀሰተኛ መረጃዎች የሚያቀርቡት የጁንታው ርዝራዦች እንዲሁም ቀደም ሲል በጁንታው ሲረዱ የነበሩ አሁን ደግሞ ጥቅማቸው የተቋረጠባቸው አካላት ይሆናሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

በባለፉት ጊዜያት በሁለት ዙር ባደረጓቸው የመስክ ምልከታዎች ደካማ ጎኖች ብለን በለየናቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተናል ያሉት ሰብሳቢው፣ አሁን ችግሮቹ ምን ያህል ተቀርፈዋል የሚለውን በአካል ለማየት በዚህ ሳምንት የመርማሪ ቦርዱ አባላት ወደክልሉ እንደሚሄዱም ጠቁመዋል።
(ምንጭ፡- ኢ ፕ ድ )