ከንቲባዋ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የአንድነት ማሳያ ነው አሉ

ግንቦት 21/2014 (ዋልታ) የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የሰላም፣ የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

“አዲስ አበባ የሰላምና የአብሮነት ከተማ” በሚል መሪ ቃል ከተማ ዐቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በወቅቱ የተገኙት ከንቲባዋ አዲስ አበባ ምንጊዜም ቢሆን ለሥርዓት አልበኝነት እና ለመከፋፈል ምቹ አይደለችም በማለት ወጣቶችም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስታደርጉ ከተማችን ለስርዓት አልበኝነት አትመችም፣ አብሮነቷ ይቀጥላል፣ አንድነቷ ያብባል እያላችሁ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የምታኮራን እንድትሆን እናደርጋታለን ያሉት ከንቲባዋ ይህንንም ማንም ሊያስቆመን አይችልም፣ ልጆቿ በትጋት እንሰራለን ብለዋል፡፡

ጤናማ፣ ብቁና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ስፖርት ያለውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት እንዲሁም ስፖርትን በኅብረተሰቡ ዘንድ ባህል ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በየሳምንቱ በቋሚነት እያዘጋጀ መሆኑን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡