ከአሸባሪው ቡድን ነፃ የወጡ ደብረ ሲና እና ሌሎች የአካባቢው ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት አገኙ

ኅዳር 25/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ነፃ የሆኑ ከተሞችንና የገጠር አካባቢዎችን እንደገና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡

በዚሁ መሰረት ደብረ ሲና፣ ጣርማ በር፣ የለን፣ ተሬ፣ ራሳ፣ ኩማሜ እና በሸዋ ሮቢት ዙሪያ ያሉ ሌሎች የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል አግኝተዋል፡፡

ወራሪው የትሕነግ ቡድን ሰሜን ሸዋ ዞን በገባበት ወቅት የወደሙና የተጎዱ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በመጠገንና መልሶ በመገንባት ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ለማድረግ የደብረ ብርሃን ዲስትሪክት ሰራተኞች ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው፡፡

በዚህም የመካከለኛ እና የዝቅተኛ መስመር ፍተሻና ጥገና ተጠናቆ የተጠቀሱት አካባቢዎች ኤሌክትሪክ ማግኘታቸውን የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር ሙሉጌታ ደሳለኝ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በወራሪው ቡድን ምክንያት ኤሌክትሪክ ተቋርጦባቸው ከቆዩ ከተሞች መካከል ሸዋሮቢት ከተማና በደብረ ሲና አካባቢ ያሉ አርማንያ፣ አስፋቸውና ጭራ ሜዳ የተባሉ የገጠር ከተሞች ቀደም ብለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘታቸውን ዋልታ መዘገቡ ይታወሳል፡፡