ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 37 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

ሚያዝያ 28/2014 (ዋልታ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 37 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል በማሳደግ ገቢውን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይህን ያለው በደቡብ ሱዳን የኢነርጂና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ ናስር የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያን “ብሔራዊ ኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል” በጎበኘበት ወቅት ነው።
በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈፃሚ አንዷለም ሲያ፤ ኢትዮጵያ ያላትን የተሻለ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለደቡብ ሱዳን ልዑኩ ማሳየት መቻሏን ገልጸዋል።
ጉብኝቱም ሁለቱ ሀገራት በሀይል መሰረተ ልማት በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያም በመጀመሪያው ምዕራፍ እስከ ሶስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለደቡብ ሱዳን 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያቀደች ሲሆን በሂደት ደግሞ ከ400 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ለማቅረብ ይሰራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ 254 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳንና ጂቡቲ እያቀረበች መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ለጎረቤት ሀገራት ከሚቀርብ ኃይል ሽያጭ በዓመት እስከ 50 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የደቡብ ሱዳን የኢነርጂና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ አገራቸው ከኢትዮጵያ የምታገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢኮኖሚ እድገቷ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግም ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችላትን ስምምነት እንዲደረስ ልዑካቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የስራ ጉብኝት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል መህዲ፤ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ግዥ ስምምነት እንድትፈጽም የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ምጣኔ ኃብታዊ ተጠቃሚነት ለማሳዳግም በኃይል፣ በመንገድና ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ለማስተሳሰር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሁለቱ ሀገራት ያካሄዱት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ረቂቅ ሰነድ ላይ ምክክር በማካሄድ የመግባቢያ ስምምነት ይፈራረማል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ለታንዛንያ፣ ሩዋንዳና ቡሩንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በኃይል መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በትኩረት እየሰራች እንደሚገኝ ተገልጿል።