ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የቀረጥና ታክስ ማሻሻያ መመሪያ ይፋ ሆነ

ሐምሌ 30/2013 (ዋልታ) – የአምራች ዘርፉን በመደገፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል የሸቀጦች አመዳደብ ሥርዓት እውን የሚያደርግ የቀረጥና ታክስ ማሻሻያ መመሪያ ማሻሻያ ይፋ ሆኗል፡፡
መመሪያው ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሁም ከጉምሩክ ኮሚሽን በተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች በተቋቋመ የታሪፍ ኮሚቴ የተዘጋጀ ሲሆን የቀረጥና ታክስ ማሻሻያው ከ8 ሺ በላይ የሆኑ ጥሬ እቃዎችን፣ ሸቀጦችንና የካፒታል እቃዎችን የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡
የግብርናና የአምራች ዘርፉን በመደገፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችልው የቀረጥና የታክስ ማሻሻያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት እንዲቻል የሀገር ውስጥ አምራቾች ከታሪፍ አንፃር ከውጭ ከሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች አኳያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ሁለት ስልቶች ተነድፈዋል፡፡
አንደኛው የምርቱ ዓይነት በሀገር ውስጥ በሚፈለገው መጠንና ጥራት የሚመረት ከሆነ ከውጭ በሚገባው ተመሳሳይ ምርት ላይ ከፍተኛ የታሪፍ መጣኔ በመጣል የሀገር ውስጥ ምርት ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
ሁለተኛ ደግሞ ምርቱ በአገር ውስጥ በብቃት የማይመረት ከሆነ ከውጭ በሚገባው ተመሳሳይ ምርት ላይ ከፍተኛ የታሪፍ መጣኔ ቢጣል የምርት እጥረት በማስከተል የዋጋ ንረት የሚያስከትል በመሆኑ እነዚህን ምርቶች በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ አምራቾች ምርት ለማምረት የሚጠቀሙባቸው በሀገር ውስጥ የማይገኙ ግብአቶች በዝቅተኛ የታሪፍ መጣኔ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ ማድረግ ነው፡፡
መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ከ8ሺህ በላይ የሸቀጥ አመዳደብ ስርአትን የያዘ የታሪፍ መለያ ዝርዝር ኮዶችን የያዘ የታሪፍ ጥራዝ የተዘጋጀ ሲሆን የቀረጥና ታክስ ማሻሻያው ለኢኮኖሚ ልማትና ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል መባሉን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘኘው መረጃ ያመለክታል፡፡