ከዚህ በኋላ የትኛውም ጠላት ኢትዮጵያን ለመድፈር አይሞክርም – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) “ከዚህ በኋላ የትኛውም ጠላት ኢትዮጵያን ለመድፈር አይሞክርም” ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
በህዝብ ኃይል ከስልጣን ተገፍቶ የወጣው አሸባሪው ሕወሓት ከውጭ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ፕሮጀክት ቀርፆ የሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የሽብር ቡድኑ “እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት” ብሎ በማቀድ ከህፃናት እስከ አዛውንት ለዘመቻ አሰልፎ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቸውን ባልተገባ ሁኔታ ለመጫን የሚሹ የውጭ ኃይሎች ደግሞ የአሸባሪውን እኩይ ዓላማ ደግፈው ቆመዋል።
ኢትዮጵያ በትክክለኛ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን የጠቀሱት አስተባባሪው ክብሯንና ነፃነቷን አስጠብቃ በመዝለቅ በፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካ የነፃነት ትግል ፊት አውራሪ ሆና ትቀጥላለች ብለዋል።
ያለፉት 3 ዓመታት የኢትዮጵያ ትክክለኛ የለውጥ ሂደትና የብልጽግና ራዕይ ያልተመቻቸው የውስጥ ከሃዲዎችና የውጭ ኃይሎች ሊያደናቅፏት በጥረት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ሆኖም ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ክብርና ሉአላዊነት ጠላቶችን በጋራ ክንዳቸው በመመከት አይበገሬነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ለአገራቸው እያሳዩት ያለው ጀግንነትና የድል ግስጋሴ “ከዚህ በኋላ የትኛውም ጠላት ኢትዮጵያን ለመድፈር የሚሞክር አይመስለኝም” ሲሉም አክለዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ የሚያሴሩ ጣላቶች ኢትዮጵያ የማትደፈር የበርካታ ጀግኖች አገር መሆኗን ሊገነዘቡ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ፈተና በጀግኖች ልጆቿ የተባበረ ክንድ ታልፈዋለች፤ በፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካ የነፃነት ትግልም ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።