ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ ታጣቂዎች ኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ እየተሰራ ነው ተባለ

የካቲት 7/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል በአኮቦ ወረዳ ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው ኅብረተሰቡ ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርሱ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን የወረዳዉ አስተዳደር አስታወቀ።

በሙርሌ ታጣቂዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጓል።

የአኮቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ኮንግ ጋትዮቴ እንዳሉት ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙሩሌ ጎሳ ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜያት ድንበር አቋርጠዉ በመግባት ጥቃት ሲፈፅሙ ቆይተዋል።

በዚህም ታጣቂ ቡድኑ ህፃናትንና የቁም እንስሳትን ሲዘርፉ እንደነበር ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀትና የስጋት ቀጣናዎችን በመለየት መሰል ጥቃት እንዳይፈፀም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋትቤል ሙን በበኩላቸው ቀደም ሲል በአከባቢው ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልፀዋል።

በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ከ2 ሺሕ 500 በላይ ወገኖች የ2 ሚሊዮን ብር 600 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

ተፈናቃይ ወገኞችም ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስም መንግሥት ድጋፉን መቀጠል አለበት ማለታቸውን ከጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡