ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም እያስጠበቁ መሆኑን የሀረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

ኅዳር 7/2014 (ዋልታ) በሀረር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው የአካባቢያቸውን ሰላም እያስጠበቁ መሆናቸውን ገለፁ፡፡
የሀረሪ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በከተማው ማህበረሰብ እየተከናወኑ የሚገኙ ሰላምን የማስጠበቅ ስራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
‘’እኔም የሰፈሬ ፖሊስና የሰላም ዘብ ነኝ’’ በሚል በከተማው በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ሲያስጠብቁ የነበሩ ነዋሪዎች ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያችንን ሰላም እያስጠበቅን እንገኛለን በለዋል፡፡
ኅብረተሰቡም መታወቂያ በሚጠየቅበት ወቅት ተገቢውን ትብብር እያደረገና እያከናወኑት ያለው ስራ እየደገፈ መሆኑን ጠቁመው አጠራጣሪ ጉዳዮችን በሚገጥሙ ወቅትም ለፀጥታ አካላት አሳልፎ እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ወጣቱ በላቀ ተነሳሽነት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመው ባከናወኑት ተግባርም ህገወጥ እንቅስቃሴና ተግባር እየተቀረፈ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
የሀረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ዋደራ እንደተናገሩት ምልከታ ባደረግንባቸው የከተማው ወረዳዎች ህዝቡ ተደራጅቶ አካባቢውን እየጠበቀ መሆኑን ተመልክተናል፡፡
በቀጣይም ህዝቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ አንፃር እያከናወነ የሚገኘውን አበረታች ተግባራት ማጠናከርና ፀጉረ ልውጦችን ማጋለጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነስሪ ዘካሪያ ወጣቱ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡