ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች ይቀርባል ተባለ


ሚያዝያ 9/2014 (ዋልታ)
ግብርና ሚኒስቴር በ2014/15 ምርት ዘመን ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ አስታወቀ።

ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ በቀጣይ ሳምንት ጀመሮ ወደ አገር ውስጥ መግባት እንደሚጀምርም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ግብርና ሚኒስቴር በ2014/15 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በዚህ ዓመት 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን የተጠቆመ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 4 ሚሊዮን ኩንታሉ እስካሁን ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በምርት ዘመኑ 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ፍላጎት መኖሩን ጠቁመው በምርት ዘመኑ ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

እስካሁን ያልገባውና በተደጋጋሚ ጨረታ የወጣው ከፍተኛ መጠን ያለው የዩሪያ ማዳበሪያም ጅቡቱ ወደብ እየደረሰ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ሳምንት ወደ አገር ቤት መግባት ይጀምራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ያብባል አዲስ በበኩላቸው እስካሁን 4 ሚሊዮን ኩንታል ከወደብ ወደ አገር ቤት እየተጓጓዘ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ያገመጠው የፀጥታ ችግር፣ በአውራጅ እና ጫኝ በኩል የተፈጠረ የተጋነነ ዋጋ፣ ሕገ-ወጥ ኬላዎች፣ መጋዘን ላይ በፍጥነት ያለማራገፍ ከገጠሟቸው ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።