ከ17 ሺሕ በላይ የክላሽ እና የሽጉጥ ጥይት ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር ተያዘ

ሐምሌ 23/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ በህግ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ከ17 ሺሕ በላይ የክላሽ እና የሽጉጥ ጥይት ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ህገ ወጥ መሳሪያዎቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ሃና ማርያም አካባቢ በቶዮታ ተሽከርካሪ ሲጓጓዙ ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረጉት ክትትል የታየዙት፡፡
በዚህም 11 ሺሕ 275 የክላሽ ጥይት፣ 6 ሺሕ 494 የሽጉጥ ጥይት፣ 11 የተለያዩ መሳሪያዎች ፣ በባለሙያ የተፈታቱ 9 የብሬን ሰደፍ፣ 4 የብሬን ተመላላሽ ሽቦ፣ 6 የብሬን ተመላላሽ ዘንግ፣ ልዩ ልዩ የክላሽ ኮቭ ጠብመንጃ አካሎች ፣ ዝናር ፣ ብዛቱ 37 የሽጉጥ ካርታ ከሌሎች የጦር መሳሪያዎች ጋር መያዛቸው ተገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B-01563 አ/አ ቶዮታ ሎንግ ቤዝ በሆነ ተሽከርካሪ 465 የስታር ሽጉጥ ጥይት እና 1 ኢኮልፒ ሽጉጥ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
የጦር መሳሪያዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙት ሦስት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የተገለጸው፡፡
ተቋማቱ ከዚህ በፊት ባደረጉት የጋራ ቅንጅታዊ ሥራ ለከተማዋ ሰላምና ደህንነት ከፍተኛ ስጋት የሆኑ ተቀጣጣይና ተተኳሽ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶችን በቁጥጥር ስር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚገባው ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና ጥይት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የሕዝብ የነቃ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሰረት በመሆኑ መሰል ህገ ወጥ ተግባራት ሲመለከት ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት ቀና ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡