ከ3 ሺህ በላይ ተተኳሽ ጥይቶች በወልዲያ ጉምሩክ ሊያሳልፉ የሞከሩ አራት ግለሰቦች ተያዙ

በወልዲያ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከ3 ሺህ በላይ የተለያዩ አይነት ተተኳሽ ጥይቶችን ሲያጓጉዙ የነበሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በጉምሩክ ኮሚሽን የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡

በቅርንጫፉ የደንበኞች ትምህርት ቡድን አስተባባሪ አቶ አሳምነው አዳነ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቅርንጫፍ ጉምሩክ ጣቢያው በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ጥይቶቹና ተጠርጣሪ ግለሰቦች ተይዘዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ኮድ 3 – 01470 አፋ በሆነ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ጭነው ከቆቦ መስመር ወደ አፋር ክልል ሲጓዙ ህዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት በጣቢያው ተቆጣጣሪዎች መያዛቸውን ተናግረዋል።

በተደረገው ፍተሻም 1 ሺህ 941 የብሬን፣ 1 ሺህ 132 የክላሽ፤ 5 የብሬን ሽንሽን ጥይቶችና 3 የክላሽ ካዝና መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

አሽከርካሪውን ጨምሮ በዚሁ ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ መታየት መጀመሩን አብራርተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደበኛ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስና የጉምሩክ ሰራተኞች ላደረጉት የተቀናጀ ጥረት አቶ አሳምነው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአካባቢው መሰል የህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ዝውውር እንዳይደረግ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንዳለ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡