ከ6 ሺሕ በላይ የክላሽ ጥይት እና የብሬን ዝናር በቁጥጥር ስር ዋለ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) በተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ ከ6 ሺሕ በላይ የክላሽ ጥይት እና የብሬን ዝናር ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

መነሻውን ባሕርዳር ከተማ ያደረገ የሰሌዳ ቁጥር 04240 ኮድ 3 አ.ማ ላንድ ሮቨር ተሽከርካሪ አካል ውስጥ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ የገባ ብዛቱ 6ሺሕ 985 የክላሽ ጥይት እና እያንዳንዱ 492 የብሬን ጥይት መያዝ የሚችል አራት የብሬን ዝናር ነው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡

ይህም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው አዲሱ ገበያ ድል በር አካባቢ ታኅሣሥ 9  ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር እጅ ከፍንጅ እንደተያዘ ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ያስታወቀው፡፡

ጥይቱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች እና ለህገ-ወጥ ተግባር የተገለገሉበት አንድ ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው እየተጣራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ስጋት ውስጥ ለመጣል እየሰሩ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውሶ የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ህገ-ወጥ ተግባር በማጋለጥ ኅብረተሰቡ ለፀጥታ አካለት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡