ካናዳ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደምታግዝ ገለጸች

ሚያዚያ 5/2014 (ዋልታ) ካናዳ በኢትዮጵያ ጠንካራ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት፣ የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደምታግዝ ገለጸች።

በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ስቴፋኒ ጆቢን ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር እንድታልፍ ካናዳ እገዛ እንደምታደርግ አረጋግጠው የኢትዮጵያን የተለያዩ የልማት ጥረቶችም ትደግፋለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለሚካሄደው አገራዊ ምክክር ካናዳ በአዎንታዊ ጎኑ እንደምትቀበለውና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ታምናለችም ኘው ያሉት።

ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታና በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ሁሉን ዐቀፍና ግልጽ የፖለቲካ ሂደቶች ሊኖሩት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙትን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የተጠያቂነትና የፍትህ ሥርዓት ገቢራዊ ማድረግም ወሳኝ መሆኑን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

እ.አ.አ ከ2021 እስከ 2022 በኢትዮጵያ ጦርነቱን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ችግር ላይ የወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ የሚውል 43 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች መሳካት የሚያግዝ 74 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በቅርቡ የካናዳ መንግሥት ይፋ ባደረገው ስደተኞችን የማቋቋም መርኃ-ግብር በመታገዝ በኢትዮጵያ ስደተኞችና ተቀባይ ማኅበረሰቦችን የትምህርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ኢዜአ አስነብቧል።