ክልሉ ለቦረና ድርቅ ተጎጂዎች እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ በተከፈቱ የባንክ አካውንቶች ገቢ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

የካቲት 21/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ለቦረና ድርቅ ተጎጂዎች እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ ለዚሁ ዓላማ በተከፈቱ የባንክ አካውንቶች ገቢ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

ክልሉ በቦረና ዞን በድርቅ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት ለመቀነስ ብዙ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል፡፡

በሀገር ውስጥ እና በውጪ ያሉ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ ታዋቂ ሰዎች እና ድርጅቶች በድርቅ ሳቢያ ለችግር ለተጋለጠው የቦረና ህዝብ እርዳታ እያሰባሰቡ መሆናቸውን አስታውቆ እያደረጉ ላለው ጥረት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

ይሁን እንጂ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ይህንን ጉዳይ ለማቀናጀት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ድጋፉን የሚያስተባብር መዋቅር የዘረጋ መሆኑን አስታውቆ ለድጋፉ ገንዘብ የሚሰበሰብበት የሂሳብ ቁጥር የተከፈተ በመሆኑ እና እየተሰበሰበ ያለው ድጋፍ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ባለው መልኩ እንዲሰበሰብ ብሎም ተጋላጩ ህዝብ ጋር እንዲደርስ በተለያየ አቅጣጫ ለተጎጂው ህዝብ እየተሰበሰበ ያለውን ገንዘብ ከዚህ በመቀጠል ባለው የባንክ የሂሳብ ቁጥር እንዲስያገቡ መጠየቁን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይፋ የተደረጉ የቡሳ ጎኖፋ የሂሳብ ቁጥሮችም በሲንቄ ባንክ፡ 1029565101201 እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000007343756 መሆናቸው ተገልጿል፡፡