ክልሉ ለ837 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

ሚያዝያ 14/2014 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ837 ህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ለሰላምና ልማት እንዲሁም ለማኅበራዊ ደኅንነት ተግቶ በመስራት ማኅበረሰቡን መካስ እንደሚጠበቅባቸው ቢሮው አሳስቧል፡፡

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ተክሌ በዛብህ በሰጡት መግለጫ የይቅርታ ሂደቱ በወንጀል ሕጉ ላይ የተቀመጠውን የይቅርታ አዋጅ መርህ ተከትሎ የተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ታራሚዎቹ ከተወሰነባቸው የእስራት ጊዜያት መካከል አንድ ሦስተኛውን ማጠናቀቃቸውን በተለያዩ ደረጃ በሚገኙ የህግ አካላትና በክልሉ ይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ የቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በማረሚያ ተቋማት በሚቆዩበት ወቅትም በየጊዜው በተለያዩ የሕግ አካላት የሚሰጠውን የማነጽ ተግባራት በተገቢው ተቀብለው የባህሪ ለውጥ ማሳየታቸው የተመስከረላቸው እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡

በይቅርታ አዋጅ ውስጥ የማይካተቱ የወንጀል ፍርደኞች መኖራቸውን ያስረዱት የቢሮው ኃላፊው ለአብነትም ከፌዴራል ማረሚያ ተቋም በአደራ እንዲቆዩ የተደረጉ በክልሉ የይቅርታ ቦርድ የማይታዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይቅርታ ተጠቃሚ የሆኑ ታራሚዎች በቆይታቸው የተሰጣቸውን የማነፅ ትምህርት በተገቢው በተግባር ላይ በማዋል ኅብረተሰቡን መካስ እንደሚጠበቅባቸው ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!