ክልሉ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፍቃድ ሰጠ

ሐምሌ 4/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 89 ባለሃብቶች ፍቃድ መስጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የክልሉ ኢንቨስትመንት፣ ማእድንና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሀመድ ያህያ በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንትን ዘርፎች ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ለገቡ ባለሀብቶች የድጋፍና የክትትል የማድረግ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት 129 የተለያዩ ፕሮጀክቶች በባለሃብቶች አማካኝነት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በተደረገ ቁጥጥርና ክትትልም ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ 17 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ወደ ሥራ ያልገቡ 18 ባለሀብቶችም ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም አብራርተዋል ።
በቀጣይም የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ በማይገቡ ባለሀብቶች ፍቃዳቸውን እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው በክልሉ በሆቴል ኢንቨስትመንት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት በተለይም በቱሪዝም ዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ይቀርፋል ሲሉ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።