ክልሉ የህዝብን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

የካቲት 10/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህዝቡን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ለ6ኛው የጨፌ ኦሮሚያ 2ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ የ2015 የግማሽ ዓመት የስራ ክንውን ሪፖርት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ፣ ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም አፍራሽ ተልዕኮ ይዘው የህዝቦችን አንድነት ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ኃይሎች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል።

የጥፋት ኃይል የሆኑት ሸኔ እና መሰሎቹ ላይ ከአጥፊ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚወሰደው ጠንከር ያለ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አክለውም በህዝብ ስም በመደራጀት የክልሉን ነዋሪ ስጋት ውስጥ ለማስገባት እና የኦሮሞን ባህልና መልካም እሴቱን ለማጠልሸት ጠላቶች ቢሰሩም የክልሉ መንግስት ከነዋሪው ጋር በመሆን አበረታች ስራ መሰራቱን ነው ያነሱት።

የኦሮሞን እና የአማራን ህዝብ ለማጋጨትና አለመተማመን እንዲኖር ጠላቶች ቢሰሩም አዳማና እና ባህርዳር ከተማ ላይ የህዝብ ለህዝብ ውይይት እንዲካሄድ በማድረግ የጠላት ህልም እንዳይሳካ ማድረግ እንደተቻለም በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።

ሰላም በማስከበር ሂደቱ ውስጥም የክልሉ ህዝብ በጉዳዩ ላይ ለራሱ በቀጥታ ከመሳተፍ አንስቶ ልጆቹን እስከ መስጠት የሚደርሱ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሚልኪያስ አዱኛ (ከአዳማ)