ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – ለትግራይ ክልል የሚውል ሰባዓዊ ድጋፍ የጫኑ 47 ከባድ ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀሌ ነገ እንደሚጓዙ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓለም ምግብ ፕሮግራምና ሌሎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በኩል ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የእርዳታ አቅርቦቶች በተገቢው መንገድ ወደ መቀሌ እንዲያጓጓዙ መንግስት ሁኔታዎችን አመቻችቷል።
በዚሁ መሰረት ነገ ከአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ 47 ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ የሚጓጓዝ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 22 ከባድ ተሽከርካሪዎች 7 ሺህ 649 ኩንታል የምግብ አቅርቦት የጫኑ ናቸው።
ቀሪ ተሽከርካሪዎች ደግሞ 7 ሺህ 300 ኩንታል የሚሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን እንደጫኑም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የግብርና ሥራዎች ለማፋጠን 10 ሺህ 359 ኩንታል ምርጥ ዘር በ12 ከባድ ተሽከርካሪዎች ለማጓጓዝ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ለቀረበ ጥያቄ ፈቃድ መሰጠቱንም አመልክተዋል።
መንግስት የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሚሰጡትን እርዳታ እንዳይስተጓጎልና በወቅቱ እንዲደርስ ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፤ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት በቀጥታ በረራ በማድረግና ከአውሮፕላን ላይ በመጣል እርዳታውን የማቅረብ ጥያቄ እንዳላቸው አብራርተዋል።
ሆኖም የቀጥታ በረራም ሆነ ከአውሮፕላን ላይ እርዳታ መጣል የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመዋል።
በተባበሩት መንግስታት ለሰብዓዊ ድጋፍ የአየር በረራ አገልግሎት እንዲፈቀድ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የሰው ኃይላቸውን ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ይዘው እንዲሄዱ መፈቀዱን አስታውሰው፤ በማንኛውም ሁኔታ “ልዩና የቀጥታ በረራ” የሚባል ፈቃድ እንደሌለ ተናግረዋል።
በአየር ትራንስፖርት እንዲጓጓዝ በማድረግ ሉዓላዊነትን የሚጥስ ድርጊት እንደማይፈቀድም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።
እስከ አሁን በክልሉ ከተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ውስጥ 70 በመቶ በመንግስት ሲሸፈን፤ 30 በመቶው ደግሞ በእርዳታ ሰጪ አጋሮች መሸፈኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ በወቅቱ እንዲደርስ 400ሺ ኩንታል የምግብ እህልና አልሚ ምግቦችን በመቀሌ በመጋዘን ማስቀመጡን የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።
የግብርና ሚኒስቴርም የተናጠል ተኩስ አቁም እስኪያደርግ ድረስ ለመኸር እርሻ የሚሆን 617 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ማስገባቱን ማስታወቁም እንዲሁ።
የዓለም አቀፍ ተቋማት አገሪቷ ባስቀመጠችው አቅጣጫ መሰረት በተገቢው መንገድ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርሱ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውም ተገልጿል።
በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት ወደ ትግራይ የተላከው የምግብ እህልና አልሚ ምግቦች በክልሉ በተከሰተው ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ይከፋፈላል ተብሎ ይጠበቃል።