ኮሚሽኑ ከመንግስታቱ ድርጅት ኤች.አይ.ቪ ፕሮግራም ጋር በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

መጋቢት 10/ 2013 (ዋልታ) – የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤች.አይ.ቪ ፕሮግራም ጋር በትብብር መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት  መፈራረማቸውን አስታወቀ።

ለኤች.አይ.ቪ ኤድስ የተሻለ ምላሽ ለመስጠትና ለመቆጣጠር አስፈላጊ እና ጠንካራ አጋርነት በመፍጠር በትብብር መስራቱ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ነው የተገለፀው፡፡

ስምምነት የፈረሙት ሁለቱ ድርጅቶች በ2030 በኤች.አይ.ቪ ኤድስ፣ ቲቪና ወባን ለመቆጣጠር በጋራ በመሆን ውጤታማ ስራዎች እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮች እና ማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር አሚራ ኤልፋዲል መሐመድ እና የመንግሳታቱ ድርጅት ኤድስ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ቢያኒያማ ተፈራርመዋል፡፡

የስምምነት ፊርማውን ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ በ2030 ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ከአፍሪካ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ትኩረት ሰጥተው በጋራ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

ኮሚሽነሯ አሚራ ኤልፋዲል የተባበሩት መንግስታት ኤዲስ ፕሮግራም  ሁሉም ባለድርሻ አካላት በፖሊሲ ማዕቀፎቻችን ውስጥ በተቀመጠው መሠረት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እና ዒላማዎች ተግባራዊነት ለማስማማት የተደረገው ከፍተኛ ጥረት አድንቀዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ የሆነው ኤች.አይ.ቪ ኤድስን ጨምሮ ሳንባ ነቀርሳን እና ወባን በ2030 ከአፍሪካ ለማጥፋት የሚሰራው ስራ ለማሳካት በትጋት እንደሚሰሩ መግለፃቸውን የአፍሪካ ህብረት በድረ-ገጹ አስነብቧል።