ኮቪድ-19 ከመከላከል ጎን ለጎን ለኤች አይ ቪ ኤድስ የሚሰጠው ትኩረት ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ሰኔ 10/2013 (ዋልታ) – ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል የሚሰጠው ትኩረት እና ጥንቃቄ ሊጠናከር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ የኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት አስገነዘበ።

ጽህፈት ቤቱ ከኮቪድ-19 መከላከል ጎን ለጎን ኤች አይ ቪ ኤድስን መከላከል በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ከመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር በቢሸፍቱ መክሯዋል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አማካሪ ወይዘሮ ዝማም ተበጀ በወቅቱ እንዳሉት ዓላማችን በኮሮና ክስተት ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየው የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ጥንቃቄ ሊነቃቃ ይገባል።

“ዓለማችን የኮሮናን ቀውስ እየስተናገደች ቢሆንም የኤች አይ ቪ ቫይረሰ ስርጭትም አልቀረላትም” ብለዋል።

“እየተዋጋን ያለነው ከሁለቱም ገዳይ ቫይረሶች ጋር ነው” ያሉት ወይዘሮ ዝማም “በፊት በመገናኛ ብዙሃን ተሰርቶ የባህሪይ ለውጥ ማምጣት የተቻለውን ያህል አሁንም ጉዳዩን መልሶ ማነቃቃት ይገባል” ብለዋል።

በውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በጽህፈት ቤቱ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በበኩላቸው እየተዘነጋ የመጣው የኤች አይ ቪ ቫይረሰ ስርጭት ሊያገረሽ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል።

“ቫይረሱ እንደገና አገርሽቶ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይፈጥር መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡን ማንቃት አለባችሁ” ብለዋል ሲስተር ፈለቀች።

“ቤተኛ” በሚለው የሬዲዮ ፕሮግራሟ የምትታወቀው ጋዜጤኛ ሶስና ተሰፋዬም በመድረኩ ስለ ጤና ጋዜጠኝነት የ15 አመት ተሞክሮዋን በማቅረብ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በቫይረሱ ዙሪያ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተናግራለች።

አሁንም በቫይረሱ የሚያዘውና የሚሞተው ሰው ብዙ መሆኑን ያወሱት ደግሞ የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በትረ ናቸው።

“መገናኛ ብዙሃን በአግባቡ ከሰሩ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ሀገራችን በዘርፉ ጥሩ ተሞክሮ አላት” ያሉት አቶ ዳንኤል በየደረጃው ያሉት አመራሮችም ጉዳዩን አጀንዳ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የቫይረሱ ስርጭት ሁኔታ እና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት በተደረገበት የአንድ ቀን የውይይት መድረክ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡