ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በአሸባሪው ሕወሓት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ፕሮግራም አስተባባሪ ሳሙኤል ከተማ ተቋሙ በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍና ለችግሮቹ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።
የምግብ እና የንፁህ መጠጥ ውኃ እጥረት፣ የፈረሱ ቤቶችን ለማደስ እና የፋብሪካ ምርቶችን ለማቅረብ ሩብ ቢሊየን ብር ተመድቦ እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።
እስካሁን 50 ሚሊየን ብር ከጭልጋ ለተፈናቀሉ፣ በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው እና በደሴ እና በደባርቅ ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹ በጂሌ ጥሙጋ እና አርጡማ ፉርሲ፣ በደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች፣ በአጣዬና ሸዋሮቢት፣ በጭልጋና በላይ አርማጭሆ አካባቢዎች ይተገበራሉ ተብሏል።
በሰሜን ወሎ እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ስድስት ወረዳዎች የ21 ሚሊየን 548 ሺሕ ብር ፕሮጀክት የትውውቅ መርሃ ግብርም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
ፕሮጀክቱ ለሴቶችና ሕፃናት ግልጋሎት እንደሚሰጥ ተገልጾ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከተፈናቀሉና ከተጎዱ ዜጎች ጎን በመቆም ይህን ክፉ ጊዜ ተባብሮ ማለፍ እንደሚገባ አስተባባሪው ማሳሰባቸውን አሚኮ ዘግቧል።