ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የአንድ ቢሊየን 200 ሚሊየን ብር የልማት ስምምነት ከሁለት ክልሎች ጋር ተፈራረመ

የካቲት 19/2013 (ዋልታ)- ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አንድ ቢሊየን 200 ሚሊየን ብር ለሚያካሄደው የተቀናጀ የልማት ፕሮግራም ከሲዳማና ደቡብ ክልሎች ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

በሀዋሳ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የፊርማ ሥነ -ሥርዓት ላይ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያን በመወከል ከሁለቱም ክልሎች ጋር ስምምነቱን የተፈራረሙት የፊልድ ፕሮግራምና ስፖንሰርሺፕ አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ እሌኒ መርጊያ ናቸው።

በደቡብ ክልል ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ለሚካሄደው የልማት ፕሮግራም ስምምነት የተፈራረሙት የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አያሌው ዝና ሲሆኑ የሲዳማ ክልልን በመወከል ደግሞ የ69 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ስምምነት የተፈራረሙት ደግሞ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አራርሶ ገረመው ናቸው።

በስምምነቱ መሰረት በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና 12 ወረዳዎች ተግባራዊ በሚደረገው ፕሮግራም 2 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ፣ በሲዳማ ክልል ሁላ ወረዳ ደግሞ ከ66 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ወይዘሮ እሌኒ መርጊያ አስታውቀዋል።

በፕሮግራሙ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል ፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ አካባቢ ጥበቃ ፣ ትምህርት፣ ምግብ ዋስትና፣ የግል ንጽህና አጠባበቅ እና የሕጻናት ጥበቃ የማህበረሰብ ልማት እንደሚገኙበት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።