ወደ ትግራይ የሚጓጓዝ ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል- የዓለም ምግብ ፕሮግራም

ሐምሌ 14 /2013 (ዋልታ) – የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ መሰረት ከአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ ወደ የሰብአዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ባመሩ 10 ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጾ፣ ተሽከርካሪዎቹ እንዲቆሙ መደረጉን ይፋ አድርጓል፡፡

ጥቃቱ ከሰመራ 115 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ስፍራ መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ሁኔታው በክልሉ ያለውን የምግብ አቅርቦት እጥረት ላይ ተጨማሪ ጫና  ያሳድራል ተብሏል፡፡

ድርጅቱ ከጥቃቱ በስተጀርባ ማን እንዳለ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመሆን እያጣራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ቅዳሜ ዕለት ባወጣው ዘገባ ለጥቃቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ቡድን ተብሎ የተሰየመውን ህወሃት ተጠያቂ አድርጓል፡፡

የአካባቢው ደህንነት እስኪረጋገጥ እና አሽከርካሪዎች በሰላም መንቀሳቀስ እስኪችሉ ድረስም ከሰመራ ሁሉም የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል የሚገኙትን ሁለት ድልድዮችን ከአገልግሎት ውጭ እንዳደረገ ከተገለጸ ጊዜ ጀምሮዳ ትግራይ የሚደረግ የሰብአዊ እርዳታዎች በአፋር ክልል እንደሚያልፉ ይታወቃል፡፡  በዚህም የተነሳ ከሰመራ ወደ ትግራይ የሚወስደው መንገድ ለሰብአዊ እርዳታ ወሳኝ  መሆኑ ይታመናል፡፡

ህወሐት የሚያስተዳድራቸው ሀይሎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻ ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ዘመቻውን ለስምንት ወራት ያህል ከቀጠለ በኋላ ፌደራል መንግስት በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ እንዳይባባስ፣ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ክልሉ ሳይገደብ እንዲደርስ እና በክልሉ የሚገኙ ዜጎች የጥሞና ጊዜ እንዲኖራቸው በማለት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

የተኩስ አቁም ውሳኔው በዓለምአቀፍ ማህበሰብ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም፣ በህወሃት በኩል ውሳኔው ውድቅ መደረጉ አይዘነጋም፡፡

በፌደራል መንግስቱ የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት ይፋ ከተደረገ በኋላ ህወሓት የትግራይ ክልል ከአማራ እና ከአፋር ክልል በሚያዋስናቸው አካባቢዎች ጥቃት እየፈጸመ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡