በማእከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ በአንድ ግለሰብ አማካኝነት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ባንክ ሊገባ የነበረ 29 ሺህ ሀሰተኛ ባለ ሁለት መቶ የብር ኖት መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የወረዳው ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኦፊሰር ዋና ሳጅን ማረልኝ አስናቀው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀሰተኛ የብር ኖቱ ትናንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሳንጃ ቅርንጫፍ ሊገባ ሲል ተይዟል።
ባንኩ ባደረገው ማጣራት ገንዘቡ ሀሰተኛ መሆኑ መረጋገጡን ተናግረዋል።
ሀሰተኛ የብር ኖቶቹን ለማስገባት ሙከራ ያደረገው ግለሰብም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ዋና ሳጅን ማረልኝ ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ ድርጊቱን በፈጸመው ግለሰብ ላይ ባደረገው ምርመራ ከወላጅ አባቱ ጋር በሬ ሸጠው ገንዘቡን እንደተቀበሉ መናገሩን አስረድተዋል፡፡
ፖሊስ የሀሰተኛ የብር ኖቶቹን ምንጭ ለመከታተል በግለሰቡ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ዋና ሳጅን ማረልኝ አመልክተዋል።
ህብረተሰቡ ገበያ ውስጥ በሚሰራጩ ሀሰተኛ የብር ኖቶች እንዳይታለል በግብይት ወቅት ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበው፤ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙም ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፈዋል፡