ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት የሞከረው አልሸባብ የሽብር ቡድን ዳግም ከፍተኛ ኪሳራ ተከናንቦ ወደ መጣበት ተመልሷል – ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የአልሸባብ የሽብር ቡድን በጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት እርምጃ ዳግም ከፍተኛ ኪሳራ ተከናንቦ ወደ መጣበት መመለሱን የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ተናገሩ።

ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ፤ ከቀናት በፊት የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በሶማሌ ክልል በአምስት ትናንሽ የጠረፍ አካባቢዎች ወደ አገር ውስጥ ሰርጎ በመግባት ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ሙከራ በጸጥታ ሃይሉ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም የጸጥታ ኃይሉ ተቆርጠው የቀሩትን የሽብር ቡድኑ አባላትን የማጽዳት ዘመቻ ሲያከናውን መቆየቱን ነው ያነሱት፡፡

ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለፉት ቀናት ከኢፌዴሪ አየር ኃይል ጋር በመቀናጀት በተወሰደው ርምጃ የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያዘጋጃቸውን የትጥቅና ስንቅ ዴፖዎች ማውደም ተችሏል፡፡ በዚህም በሽብር ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን የሽብር ቡድኑ ዛሬ ሌሊት ላይ የተበታተነ ኃይሉን በማሰባሰብ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሚዋሰኑበት አካባቢ ወደ አገር ውስጥ ሰርጎ በመግባት ጥቃት ለመፈጸም መሞከሩንም ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ተናግረዋል፡፡

ሆኖም የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ የሽብር ቡድኑ ዳግም ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራዎችን ተከናንቦ ወደ መጣበት መመለሱን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃም ከ150 በላይ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንና የሽብር ቡድኑ ለአጥፍቶ መጥፋት ያዘጋጃቸው ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን ገልጸው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እንደተማረኩ አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊትና ጥምር የፀጥታ ኃይሉ የሽብር ቡድኑን ትንኮሳዎች ለመመከት በሙሉ ቁመና ላይ መሆኑን የጠቀሱት ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ የሶማሌ ክልል ሕዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለክልሉ ልዩ ኃይል ያለውን ደጀንነት በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊትና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልን ጨምሮ የፀጥታ ኮማንድ ፖስቱ በአካባቢው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመድፈር በሚሞክር የትኛውም ኃይል ላይ እርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡