ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ላሉ ዳያስፖራዎች ፈጣን አገልግሎት እየተሰጠ ነው – የጉምሩክ ኮሚሽን

ታኅሣሥ 19/2014 (ዋልታ) የጉምሩክ ኮሚሽን አገራዊ ጥሪን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ላሉ ዳያስፖራዎች ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ገለጸ፡፡
በጉምሩክ ኮሚሽን የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የመንደኞች ጉዳይ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዘራኤል ለአ የህክምና ቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችን ይዘው የሚመጡ መንገደኞች ያመጡትን ድጋፍ በቀላሉ ለማስረከብ እንዲያመቻቸው ከጤና ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዳያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ያመጡትን የተለያዩ አገራት ገንዘቦች በህጋዊ መንገድ በመመንዘር አገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሬ እንደታገኝ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አገራዊ ጥሪን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዳያስፖራዎችም በቆይታቸው የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጤን እና ኢንቨስት በማድረግ ሰፊ የሥራ እድልን ለመፍጠር እንዲሁም ምርቶችን ወደ ውጭ አገራት በመላክ በቂ የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ እንደሚሰሩ መናገራቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡