ወጣቶች ለሰላም ያላቸውን ሚና ማጎልበት አለባቸው ተባለ

ሰኔ 18/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ‘’የኛ ዘመን ወጣት ሚና’’ በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ ከተለያዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ተወያይቷል፡፡

በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ሥራ አስፈፃሚ አባል ሮች ጎች እንዳሉት በተለይም ወጣቶች  የለውጡ ቱሩፋቶችን በአግባቡ መረዳትና ለውጡን ማስቀጠል ይገባቸዋል፡፡

ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ላይም ሚናቸውን ማጎልበት አለባቸው ብለዋል፡፡

በሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ እና የሲቪክ ማኅበራት ዘርፍ ኃላፊ ሀሰን አብዲ በበኩላቸው በክልሉ ያለው የሥራ አጥነት ችግር እንዲቀረፍ ፓርቲው በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመው ወጣቶች ከጠባቂነት ተላቀው ሥራ ፈጣሪ መሆን አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመቅረፍ አንፃር በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበው በክልሉ ከሚካሄደው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር ተያይዞም የክልሉ ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች በሰጡት አስተያየት አንድነታቸውን በማጠናከር በሀገሪቱ ሰላም እንዲጎለብት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ካለፉ ታሪኮች መልካም ተሞክሮችን በመውሰድ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባ አንስተው መንግሥትም የሥራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ በትኩረት መስራት አለበት ብለዋል፡፡