ወጣቶች በበጎ አድራጎት ስራ በመሣተፍ የወገን አለኝታነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል- አቶ ደስታ ሌዳሞ

አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – የክልሉ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሣተፍ በጅምር ላይ ያሉ የልማት ስራዎችን ማፋጠንና የወገን አለኝታነታቸውን ማሣደግ ይኖርባቸዋል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የ2013 ዓ.ም የወጣቶች የክረምት በጎ አድራጎት ስራ በይፋ አስጀምረዋል።

ርዕሰ መሥተዳድሩ የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጆች ኑሮ ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስና የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ “ኢትዮጵያን እናልብስ” በሚል መሪ ቃል እንደሀገር የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር በማሳካት ልማቱን ለማፋጠን ሁሉም የክልሉ ነዋሪ በተለይም ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም በደም እጥረት ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን ለመታደግ ደም በመለገስ እንዲሁም አቅመ ደካሞችን በመርዳት ጅምር ላይ ያሉ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን መደገፍ ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል የሴቶች ህፃናትና የወጣቶች ቢሮ ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ሀላፊ አቶ አክሊሉ አለሙ በበኩላቸው፣ በዘንድሮው የክረምት በጎ አድራጎት ስራ 540 ሺህ ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ 13 ዋና ዋና ተግባራት ላይ እንደሚሠራ ገልፀዋል።

የክረምቱ ወራት “ኢትዮጵያችንን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት አረንጓዴ ልማት እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል ችግኝ በስፋት የሚተከልበት፣ በተለይ በገጠር የሚኖሩ ወጣቶች አቅመ ደካሞችን በግብርና ስራ የሚረዱበት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጥበት እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህም 1 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግና ግማሽ ቢሊየን የመንግስትን ወጪ ለማስቀረት መታቀዱን አቶ አክሊሉ አስታውቀዋል።

በዕለቱ አጠቃላይ በሲዳማ ክልል በተለያየ በጎ ተግባር ላይ ተሰማርተው አመርቂ ውጤት ላሳዩ ሰባት ማዕከላት የክልሉ መንግስት 5 ሚሊየን ወጪ በማድረግ የማበረታቻ ሽልማት መበርከቱን ኢፕድ ዘግቧል።