ዋልታ ለተፈናቃዮች በአንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረገ


ኅዳር 11/2014 (ዋልታ) የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ከሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ለተጠለሉ ተፈናቃዮች በአንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አደረገ፡፡
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር) ድጋፉ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ዕለታዊ የምግብ ፍጆታዎችንና የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ግብዓቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ ከድርጅቱ ማናጅመንትና ሠራተኞች መገኘቱን የገለፁት ሥራ አስፈጻሚው ዋልታ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በሰብዓዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ስላለበት ድጋፉን አድርገናል ብለዋል፡፡
ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ሀገራዊ ችግሮች እንዲቀለበሱና መፍተሄ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራአስፈፃሚው አቅም ያላቸው ወገኖች ተፈናቃዮችን እንዲደግፉ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የውጭ ጫና በመመከት፣ የሽብርተኛውን ቡድን አሉባልታ በማጋለጥና ለህብረተሰቡ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ በማድረስ እንዲሁም ህብረተሰቡ በሁለንተናዊ መልኩ የኅልውና ትግሉ አካል እንዲሆን በመቀስቀስ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣም ሀገራዊ ጥቅሙን ማስጠበቅ የተቋሙ ዋነኛ ስራ መሆኑን ገልጸው ቁሳዊ ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሲሳይ ወልደ አማኑኤል በሽብር ቡድኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ ዞኑ ለመጡ ተፈናቃዮች የድርጅቱ ማናጅመንትና ሠራተኞች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ድርጅቱ የኅልውና ዘመቻውን ከተቀላቀለ ሰንብቷል ነው ያሉት፡፡
ዋልታ ህብረተሰቡ ሚዛናዊ መረጃ በማግኘት ከስህተትና ከመሸበር እንዲጠበቅ ሲሰራ ቆይቷል ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው በቀጣይም ህብረተሰቡ ትክክለኛና እውነተኛ መረጃ አግኝቶ የትሕነግን የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ከመመከትና ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የአካላዊ ጦርነቱ ተሳታፊ እንዲሆን የተጠናከረ የሚዲያ ስራ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡