ዋልታ ቴሌቪዥን በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማከራከር ጀመረ

ሚያዝያ 06/2013 (ዋልታ) – ዋልታ ሚዲያና ኮሚንኬሽን ኮርፖሬት ያዘጋጀው የመጀመሪያው የፓርቲዎች የክርክር መድረክ በፌዴራሊዝም እና ብዝሃነት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በዛሬው እለት አከራክሯል፡፡

በክርክር መድረኩ ላይ የብልፅግና፣ ኢዜማ፣ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ እና አዲስ ትውልድ ፓርቲ አመራሮች በፌዴራሊዝም እና ብዝሃነት ላይ የፓርቲዎቻቸውን አቋም አንፀባርቀው ነው ክርክሩን ያደረጉት።

ብልፅግና ፓርቲን የወከሉት አቶ ካሳሁን ጎፌ፤ ብልፅግና እውቀትንና እውነትን መሰረት አድርጎ የተመሰረተ ፓርቲ በመሆኑ ለ27 ዓመታት በፊት የነበረውን የሞግዚት ፌደራሊዝም በማስተካከል በዜጎች ነፃ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ባለፉት ሶስት ዓመታት ተጨባጭ ለውጦችን አካሂዷል ብለዋል፡፡

ፓርቲያችን ተቋማዊ መሰረት ያለው፣ ወንድማማችነትን በማዳበር ብሔራዊ መግባባት የሚሰራ፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን ማዕከል ያደረጉ ብዝሀነቶችን በማስጠበቅ እውነተኛ ህብረ-ብሔራዊ የፌደራሊዝም ስርዓትን ያረጋግጣል ነው ያሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማን ወክለው የተገኙት አቶ ኢዮብ መሳፍንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ በርካታ ብዝሀነቶችን በውስጧ የያዘች ሀገር በመሆኗ የፌደራል ስርዓትን ተመራጭ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡

አክለውም አሁን ላይ ያለው የፌደራል አወቃቀሩ ችግር የፌደራል ስርዓቱ ለክልሎች ግዛትና ወሰን ሰጥቶ ለዜጎች መፈናቀልና ግድያ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም ዜጎች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመረጧቸው ሰዎች እንዲተዳደሩ እንሰራለን ያሉ ሲሆን ብዝሀነትንም በተመለከተ መጤ እና ነባር በሚል የተፈጠረውን መከፋፈል በማስተካከል ብሔራዊ መግባባት ላይ ፓርቲያቸው በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ተወካዩ አቶ ዘኑር አብደላ ውሀብ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ባህል፣ ትፊት፣ ዕሴት እንዲሁም ጥልቅ የፖለቲካ ባህል ያላቸው ናቸው ብለን ስለምናምን ህብረ-ብሔራዊ ፌደራሊዝምን ለማረጋገጥ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በህዝቦች ነፃና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ በመረጡትና በወሰኑት የፌደራሊዝም ስርዓት እንዲተዳደሩ ይደረጋል በዚህም የክልሎችንም አደረጃጀት በተመለከተ በህዝቦችን ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እዲሆን እንሰራለን ብለዋል፡፡

አዲስ ትውልድ ፓርቲ ወክለው የተሳተፉት ክንፈ ማሪያም ሙሉጌታ በበኩላቸው የፌደራል ስርዓቱን እኔ አውቅልሀለሁ ከሚል ሽንገላ አላቀን ዜጎች በመረጡትና በፍላጎታቸው እንዲተዳደሩ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

በፌደራሊዝም ከመነገድ ይልቅ የስርዓቱን ጠቃሚነት ህዝባችን እንዲገነዘቡትና እንዲያውቁት እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ብዝሀነትን አካታች ያደረገ የፌደራል ስርዓት ከሀገሪቱ ዓውድ ጋር በማሰናሰል የህዝቦችን ግንኙነት በሚያጠናክር መልኩ የምንተገብረው ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በቀጣይ ድምፅ አግኝተው መንግስት ከመሰረቱ የሚከተሉትን የፌዴራል አወቃቀር በተመለከተም ክርክር አድርገዋል።

(በደረሰ አማረ)