ዓለም በከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ ትገኛለች – አንቶኒዮ ጉተሬዝ

ሐምሌ 15/2016 (አዲስ ዋልታ) በፈረንጆቹ ሰኔ ወር 2025 በስፔን ለማካሄደው የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮንፍረንስ አጀንዳ የማሰባሰብ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀምሯል።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዓለም በከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ላይ እንዳለች በማሳሰብ አዲስ አባባ እያስተናገደች ከምትገኘው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ብዙ የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚጠበቁ ገልጸዋል። በዚህም ካደጉ እና ባለፀጋ ከሆኑ አገራት ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያን የወከሉት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ችግር እና የፖለቲካ አለመረጋጋት በዓለም የተረጋጋ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ችግር እየጋረጠ እንደሚገኝ ገልጸው በዚህም አፍሪካ ትልቅ ዋጋን እየከፈለች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

በተለይም የአየር ንብረት ለውጡ ትልቁን ፈተና እየሆነ እንደሚገኝ አንስተው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርኃ ግብር ለብዙዎች መልካም ተሞክሮ መሆኑንና ለእንዲህ ላለው ተግባር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ዓለም የፋይናንስ ምንጭ ችግር የለባትም ያሉት አምባሳደር ታዬ ይህን ወደ አንድ ማምጣት እና ዘላቂ እና ፍትሓዊ የፋይናንስ ስርጭት እንዲኖር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የገለፁት።

በሌላ በኩል በዓለም ዙሪያ እተስተዋለ ለሚገኘው የፋይናንስ ችግር የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋልም ተብሏል።

በኮንፍረንሱ ላይ የበርካታ ዓለም አገራት መሪዎች ተሳታፊ እየሆኑ ይገኛሉ።

በሚልኪያስ አዱኛ