ዓለም አቀፍ የጤና ደንብ አገራት ከተባበሩ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚቻል ማሳያ መሆኑ ተገለጸ


ግንቦት 26/2016 (አዲስ ዋልታ) ማሻሻያ ተደርጎበት የፀደቀው ዓለም አቀፍ የጤና ደንብ አገራት ከተባበሩና በጋራ ከሰሩ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚቻል አይነተኛ ማሳያ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ሲካሄድ የነበረው 77ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ በ2005 ዓለም አቀፍ የጤና ደንብ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ በማጽደቅ ተጠናቋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የአፍሪካ አባል ሀገራትን በመወከል ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ማሻሸያ ተደርጎበት የፀደቀው ዓለም አቀፍ የጤና ደንብ አገራት ከተባበሩና በጋራ ከሰሩ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚቻል አይነተኛ ማሳያና ምስክርነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህንን በማበከር ደንቡ ለድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ወረርሽኝ ቅኝትና ቁጥጥር ዝግጁነት እንዲሁም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ ደንቡ ተግባራዊ እንዲሆን ላለፉት 2 ዓመታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አካላትንም አመስግነዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቡድንን በማስተባበር የጋራ አቋም እንዲያዝና በቀረቡት ማሻሻያዎች ውስጥ ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማሳደግ ለታዳጊ አገራት ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጡ ማሻሻያዎች እንዲጸድቁ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቷም ተገልጿል፡፡

የአገራትን ሉዓላዊነት የሚጋፉና በተለይም በአፍሪካ አገራት ላይ የንግድና ትራንስፖርትና ኢኮኖሚ ረገድ አስገዳጅ ግዴታዎች የሚጥሉ ሃሳቦች እንዳይካተቱ ማድረግ ተችሏልም ተብሏል፡፡

ከ300 በላይ ፕሮፖዛል በአባል አገራት ቀርቦ ማሻሻያ ተደርጎ የፀደቀው ዓለም አቀፍ የጤና ደንብ በዋናነት በህብረተሰብ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ወቅት የሀገራት ዝግጁነትና ምላሽ አሰጣጥ አቅምን ለማሻሻል እንዲሁም ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።

ተሻሽሎ የጸደቀው የዓለም አቀፍ የጤና ደንብ ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋና ወረርሽኝ ሲከሰት ፍትኃዊ የሆነ የህክምና ግብዓት ተደራሽነት እንዲኖር ይረዳልም ተብሏል፡፡

መሰረታዊ የሆኑ የህብረተሰብ ጤና አቅም ለማዳበር የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ በተለይም ለታዳጊ አገራት ለማሰባሰብ እንዲቻል አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ መሆኑም ተገልጿል።

በሌላ በኩል አገራት ለህብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲችሉ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ጠንካራ የጤና ስርዓት እንዲኖራቸው የሚያግዙ ሌሎች የመፍትሄ ሀሳቦችና ውሳኔዎች በጉባኤው ቀርበው መጽደቃቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡