ዓለም ከአይሁዳውያን ጭፍጨፋ ሊማርና ዘረኝነትን ሊፀየፍ እንደሚገባ ተገለጸ

በአይሁዳውያን ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ የሚያስታውስ የመታሰቢያ ሥነ-ስርዓት እየተካሄደ ነው።
ዓለም አቀፍ የመታሰቢያ ሥነ-ስርዓቱን በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ አምባሳደር፣ የእስራኤል ኤምባሲ አምባሳደር፣ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ተጠሪና የሌሎችም ሀገራት ተወካዮች በመገኘት እለቱን እያሰቡት ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋዬል ሞራቭ በሚሊየን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በማንነታቸው ብቻ እንዲጨፈጨፉ መደረጉን አስታውሰው፣ ከታሪክ ልንማርና ለዘረኝነት እምቢ ልንል ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴቨን ሀወር በበኩላቸው፣ በወቅቱ በአይሁዳውያን ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ የሚያሳፍር ቢሆንም፣ እለቱን ሁሌም ትውልድ እንዲያስበው ማድረግና ዳግም እንዲህ አይነት ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እንዳይደገም መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመታሰቢያ ሥነ-ስርዓቱ በወቅቱ ህይወታቸውን ላጡ አይሁዳውያን የህሊና ፀሎት ተደርጓል።
(በትዕግስት ዘላለም)