ዓመታዊው የግዮን በዓል በሰከላ እየተከበረ ነው

ዓመታዊው የግዮን በዓል

ጥር 13/2014 (ዋልታ) የአቡነ ዘርዓ ብሩክ የንግስ በዓልን አስታኮ እየተከበረ በሚገኘው በዓል ላይ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በታላቁ የዓባይ/ግዮን ወንዝ መፍለቂያ በግሽ ዓባይ ሰከላ የሚከበረው በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ መከበር ከጀመረ 4 ዓመታትን አስቆጥሯል።

የበዓሉ መከበር ዓባይ ለሀገር የሚሰጠውን ጥቅም ለማሳደግ ወንዙን ከመነሻው ጀምሮ ማልማት አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ለመስጠት ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ዓባይ ወንዝ ከሀብትነቱ ባሻገር ታሪካችን፣ ባህላችንና ማንነታችን በመሆኑ ወንዙ ከመፍለቂያው ጀምሮ እንዲለማና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በትጋት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት በዓሉ ጎልቶ እንዲከበር የዓባይ ምንጭም በቱሪስቶች በስፋት እንዲጎበኝ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ዓባይ ወንዝ ለዘመናት ጥቅም ላይ ሳይውል ቢቆይም አሁን ላይ በጉባ በመገደብ የኅብረተሰቡን ሕይወት ሊቀይር በሚችል መልኩ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ አሁንም ቢሆን ሀብቱን በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።