ዓድዋ ማሸነፍን ከፍቅር፤ ድልን ከይቅር ጋር አዋህዶ ያበሰረ የሁላችን የነጻነት ታሪክ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዓድዋ ማሸነፍን ከፍቅር፤ ድልን ከይቅር ጋር አዋህዶ ያበሰረ የሁላችን የነጻነት ታሪክ ነው

የካቲት 22/2014 (ዋልታ)ዓድዋ ማሸነፍን ከፍቅር፤ ድልን ከይቅር ጋር አዋህዶ ያበሰረ የሁላችን የነጻነት ታሪክ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ ለ126ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ዓድዋ፤የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ግርማ፤
የኢትዮጵያዉያን የአንድነት ምሰሶ፤
የማይደበዝዝ በደምና በአጥንት የተፃፈ ደማቅ ታሪክ !
እንኳን ለ126 ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!
ዳግም ዓድዋ በሚሰኙ ኢትዮጵያችንን ከመበተን የታደገ፤ ዓባይን የብርሃን ጮራ እንዲያመነጭ ያደረገ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ በአንድነት ክንዳችን የተገኙ ድሎች ታጅቦና ደምቆ የሚከበር በመሆኑ የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓል ከመቼውም ጊዜ ልዩ ያደርገዋል፡፡
የዓድዋ ጀግኖች በርግጥም በሞታቸው ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ፤ ነጻነትን ከነክብሩ አድምቀው የጻፉ ሞትን በነፃነት ድል የነሱ፤ ከአገር በላይ ምንም አለመኖሩን በግብር ያረጋገጡ ሰብዓ ግዙፋን ናቸው፡፡
ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን በተግባር ኢትዮጵያን ሆነው፤ ኢትዮጵያን አክለው መዋደቃቸው፤ ዛሬ እኛን ከአንገታችን ቀና አድርጎናል፡፡ በኩራትና በሞገስ የምንራመድ፤ የስነ-ልቦና ከፍታን የተላበስን ህዝቦች አድርገውናል፡፡
በአትዮጵያችን ፋና ወጊነት የዓለም ጥቁር ህዝቦችም ስለነፃነት ታሪክን መፃፍ ጀመሩ፡፡ ዓድዋ ይሄንን ደማቅ ታሪክ በክብር የቀደሰ ክቡር በዓላችን ነው፡፡
የዓድዋ ድል ከግዙፉ ተራራ በላይ ግዙፍ ሃገርና ህዝብ እንዳለ ለአለም ያስተማረ የፓን አፍሪካኒዝም እና የጭቁን ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ማህጸን ነው፡፡ ዓድዋ ማሸነፍን ከፍቅር፤ ድልን ከይቅር ጋር አዋህዶ ያበሰረ የሁላችን የነጻነት ታሪክ ነው::
ዓድዋ በኢትዮጵያም በአለምም ብዙ አድዋዎችን ወልዷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው የውጪ ወራሪዎች በምንም ሁኔታና አቅም ቢመጡ አንገት ማስደፋትና መመለስ የሚችሉ ጀግና ህዝቦች መሆናቸውን በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
ዛሬ ስለ ዓድዋ ስንናገር ስለበርካታ አድዋዎች ስንቅ ለመሰነቅም ጭምር ነው፡፡ ዓድዋን የምንተርክ ብቻም ሳንሆን ዓድዋን ኢትዮጵያን ለማበልፀግ ግዙፍ ሃሳብና ትልም የምናሳካበት መሆኑን በሚገባ እናውቃለን!!
ውድ የከተማችን ነዋሪዎች ጥቃቅን ልዩነቶችን በማጉላት በዚህ ታሪካዊ በዓል ላይ ሳይቀር የሚከፋፍል አጀንዳን ለመፍጠርና ልዩነትን የሚያጎሉትን ትተን እንደ አባቶቻችን ተልቀን፤ ኢትዮጵያን አክለን በአንድነት እንድናከብር ጥሪዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵዊያን፣ ለአፍሪካም ሆነ የመላ ጥቁር ህዝብ የኩራት ምንጭ ለሆናችሁ ለአድዋ ጀግኖች ይሁን፡፡
መልካም የዓድዋ ድል በዓል !!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ !!