ምዕመኑ ጾመ ፍልሰታን የተቸገሩትን በመርዳትና በመተባበር ማሳለፍ እንደሚጠበቅበት ተጠቆመ

ሐምሌ 29/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ጾመ ፍልሰታን የተቸገሩትን በመርዳትና ለአገር ሠላምና አንድነት በመፀለይ አንዲያሳልፉ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ-ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አሳሰቡ።

ብጹዕነታቸው በአገር ውስጥና በመላው ዓለም ለሚገኙ አማኞች ለ2013 ጾመ ፍልሰታ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለ16 ቀናት በሚዘልቀው ጾም ፀሎተ ምህላ እንዲደረግ በሲኖዶስ መወሰኑንም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ መሰረት ከሚጾሙ ሰባት አፅዋማት መካከል ጾመ ፍልሰታ ለማርያም አንዱ መሆኑን ፓትሪያርኩ አስታውሰዋል።

ፆመ ፍልሰታ የእምነቱ ተከታዮች አዛውንት፣ ሕጻናትና ወጣቶች በተመስጦና በመንፈሳዊ ስሜት በረከትና ረድኤት ለማግኘት የሚጾሙት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።

በመሆኑም ጾሙ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማጉረስና የታረዙትን በማልበስ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ ራሱን ከኮቪድ-19 በመጠበቅ ጾሙን ለኢትዮጵያ ሠላምና አንድነት በመፀለይ እንዲያሳልፍም ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ብፁዕነታቸው አማኞች ጾሙን ሲጾሙ በቀኖና ቤተክርስቲያን መሰረት የጾም መሳሪያዎች የሆኑትን ሠላም፣ ፍቅር፣ ጸሎት ምጽዋትና ትዕግስትን በመተግበረ እንዲያሳልፉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጾመ ፍልሰታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ከነሃሴ 1 ጀምሮ በጾምና በጸሎት ለ16 ቀናት ፈጣሪያቸውን በመለመን የሚያሳልፉት ነው።