ዕርዳታ የጫኑ 20 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ገቡ

ሚያዝያ 23/2014 (ዋልታ) የዓለም ዐቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የሰብአዊ ዕርዳታ የጫኑ 20 ተሽከርካሪዎች ትግራይ ክልል መግባታቸውን አስታወቀ።

ድጋፉ የምግብ፣ የእህል ዘሮች፣ የሕክምና አቅርቦቶችን እና የውኃ ማከሚያ ቁሳቁሶች ሲሆን  በየብስ የሰብአዊ ዕርዳታ ማጓጓዝ ከተጀመረ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል።

የሕክምና አቅርቦቱ በትግራይ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ 13 የጤና ጣቢያዎች ለሚገኙ 65 ሺሕ ታካሚዎች ለ3 ወር እንዲሁም በአራት ሆስፒታሎች ለሚገኙ 6 ሺሕ 600 የስኳር ሕሙማን ለአንድ ወር እንደሚያገለግል ተነግሯል፡፡

የሰብአዊ ዕርዳታው የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ 19 የጤና ማዕከላት 20 ሺሕ ታካሚዎችን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች እና ቤተሰቦቻቸውን ለአንድ ወር የሚያገለግል የምግብ ድጋፍ ያካተተ መሆኑንም አመልክቷል።

ድጋፉ በመቀሌ፣ አዲግራት፣ ሽሬ፣ አድዋ እና አክሱም ከተሞች የሚገኙ የውኃ መሠረተ-ልማቶችን በመጠገን እና በማከም በከተሞቹ የሚኖሩ ዜጎች የንፁህ ውኃ መጠጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ተብሏል።

የውኃ መሠረተ-ልማቶች መልሶ ግንባታ በአይደር ሆስፒታል በየቀኑ ሕክምናቸውን የሚከታተሉ 500 ዜጎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ እንዲያገኙ ያደርጋል ያለው ኮሚቴው፣ የሽሬ ሆስፒታል ሕንፃ ዳግም ሥራ መጀመር በየቀኑ 100 ታካሚዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አመልክቷል።

በድጋፉ አማካኝነት በትግራይ ክልል ገጠራማ አካባቢዎች የሚተከሉት የውኃ ፓምፖች 40 ሺሕ ዜጎችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ድርጅቱ አስታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ከሕክምና እና የውኃ አቅርቦት ድጋፍ በተጨማሪ ለ15 ሺሕ ዜጎች የሚያገለግሉ የቤት ውስጥ እቃዎች እና 20 ሺሕ አርሶ አደሮች የሚሰራጩ የእህል ዘሮች እንደተካተቱበትም አመልክቷል።

ሁሉም አካላት በጣም አስፈላጊ የሆኑ የሰብአዊ ዕርዳታዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ እያደረጉት ያለውን ትብብር ያደነቀው የሰብአዊ ድርጅቱ በመደበኛነት ድጋፎች እንዲደርሱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ድጋፍ በትግራይ ክልል ከሚያደርገው በተጨማሪ በአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር በሶማሌ፣ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚገኙ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን እንስሳት ክትባት መስጠቱን አመልክቷል።