ዘመን ባስ የተፈናቀሉ ወገኖችን በነፃ ትራንስፖርት ወደ ቀያቸው መመለስ ጀመረ

ታኅሣሥ 4/2014 (ዋልታ) ዘመን ባስ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን በነፃ ትራንስፖርት ወደ ቀያቸው መመለስ ጀመረ፡፡

ዛሬ በሁለት አውቶቡስ የጀመረው አገልግሎቱ ለ10 ቀናት እንደሚቆይ ድርጅቱ ለዋልታ ገልጿል፡፡

የዘመን ባስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አይላቸው አያና በአዲስ አበባ እና በሌሎች ማቆያ ጣቢያዎች የሚገኙ የደሴ፣ የኮምቦልቻ፣ የሸዋሮቢት፣ የከሚሴ እና ሌሎች ነጻ የወጡ አካባቢ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከመንግሥት ጋር በመተባበር ነፃ ትራንስፖርትን አቅርበናል ብለዋል።

በአገልግሎቱ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለእናቶች እና ለህፃናት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያስታወቁት ኃላፊው በርካታ ወገኖች እየተዘመገቡ ነው ብለዋል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት ሜክሲኮ፣ መስቀል አደባባይ እና ላምበረት መናኸሪያ በሚገኙ የዘመን ባስ የትኬት መቁረጫ ቢሮዎች መመዝገብ የግድ እንደሆነም ገልፀዋል።