ዘምዘም ባንክ ለደንበኞቹ በተለያዩ ቴክኖሎጂ አማራጮች ተደራሽ ለመሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታወቀ

ነሐሴ 26/2013 (ዋልታ) – ዘምዘም ባንክ ለደንበኞቹ በተለያዩ ቴክኖሎጂ አማራጮች ተደራሽ ለመሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

ባንኩ እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራትና በቀጣይ 2014 ዓ.ም ስለሚሰራቸው ሥራዎች ለባለድርሻ አካላትና ለደንበኞቹ ገለፃ አድርጓል።

ግንቦት 26/2013 ዓ.ም የተመሰረተውና ወደ ስራ የገባው ዘምዘም ባንክ ላለፉት ሶስት ወራት ካከናወናቸው አበይት ተግባራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የሆነ አገልግሎት መጀመሩን አስታውቋል።

ባንኩ በአዲስ አበባ ዘጠኝ ቅርንጫፎችን በመክፈት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የገለፁት የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ መሊካ በድሪ፣ ከአዲስ አበባ ውጪ በድሬዳዋና ጅግጅጋ ቅርንጫፍ በቅርብ ቀን እንደሚያስመርቅ ገልፀዋል።

የዘምዘም ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ናስር ዲኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባንኩ አቅም እያላቸው እጃቸው ላይ ገንዘብ የሌላቸው ዜጎችን የመደገፍ ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

(በሱራፌል መንግስቴ)