የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ዩኒፎርሞችን ማምረት ጀመረ

ነሐሴ 25/2014 (ዋልታ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ወታደራዊ ዩኒፎርም (መለዮ) በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ መመረት መጀመራቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ፣ የኮርፖሬሽኑ የትራንስፎርሜሽንና ዋና ስራ አስፈፃሚ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ፍፁም ከተማ እንዲሁም ሌሎች የስራ ኃላፊዎች የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸው “ኢፒክ አፓረል “የተሰኘውንና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዩኒፎርምን እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ዩኒፎርሞችን የሚያመርት ኩባንያን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው ኩባንያው ዩኒፎርሞቹን ከሁለት ሳምንት በፊት ማምረት የጀመረ ሲሆን በምርት ሂደቱ ላይ ባሉ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ከኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ሀላፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

ከ177 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ስራውን የጀመረው ኩባንያው አሁን ላይ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ላይ በመሰማራት ከ2 ሺሕ 500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡

ሀዋሳ ኢንዱስተሪ ፓርክ ደግሞ በአሁን ሰዓት ከ20 በላይ አምራች ኩባንያዎችን በውስጡ የያዘ ሲሆን በኢትዮጵያ ካሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቀደምት ከሚባሉት የሚጠቀስ መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!