የሀገርን ሰላም ከልማት ጋር አስተሳስሮ በማስኬድ የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ

አረንጓዴ አሻራ መርኃግብር

ሰኔ 25/2014 (ዋልታ) የሀገርን ሰላም ከልማት ጋር አስተሳስሮ በማስኬድ የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር ሁሉም ማኅበረሰብ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡

በባለሀብቶችና ሥራ ፈጣሪዎች ትብብር የተመሠረተው የሰላምና የልማት ፎረም እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት በአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡

“ኑ ሰላምን እንትከል ወንድማማችነትን እናጠናክር” በሚል መሪ ቃል የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ያካሄዱት አባላቱ የሀገርን ሰላም ከልማት ጋር አስተሳስሮ በማስኬድ የበለፀገች እንዲሁም ከሰላም የተወዳጀች ሀገር ለመፍጠር ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የበኩሉን ጠጠር እንዲጥል ጠይቀዋል::

ሀገር የጀመረችውን የልማት ጎዳና ለማስቀጠል የደን ሀብታችንን ማሳደግ ይገባል ያሉት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለዚህም እንደ ሀገር የተያዘው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው በመገንዘብ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል::

የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው ልማት እንዲሁም ሰላም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገፅታ በመሆናቸው ልማታችንን ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን ማራመድ ይገባል ብለዋል፡፡

በመርኃግብሩ ላይ የፎረሙ የበላይ ጠባቂዎች የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) እና የኮሚሽኑ ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

በሔብሮን ዋልታው

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW