የሀገር ቀዳሚ የልማት ተዋናይ መንግስት ቢሆንም የሲቪል ማህበረሰቡም ከፍተኛ ድርሻ አለው -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) – የአንድ አገር ዋነኛና ቀዳሚ የልማት ተዋናይ መንግስት ቢሆንም የሲቪል ማህበረሰቡም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘዉዴ የሴቶች ወር መርሃ ግብር ማጠቃለያ በሆነዉና በሴቶች ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበራት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካፈሉበት ስብሰባ ላይ ተገኝተዉ ባሉባቸዉ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ከዚህ በፊት በጠሩት የሲቪል ማህበራት ስብሰባ ላይ የሲቪል ማህበራት ቅንጅትና ትስስር ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችን ከማሳካት ረገድ ያለዉን ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስብሰባዉ ፍጻሜም ይህንን ጥረት የሚያስተባብር አካል ተቋቁሟል ነው የተባለው፡፡

የሴቶችን ጉዳይ የበላይ ባለቤትና አስተባበሪ የሆነ ድርጅት አስፈላጊነት ላይ ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን ለተግባራዊነቱ ዝግጅት መጀመሩን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።