የሃብት ማሳወቂያና ምዝገባ ዲጂታል ሥርዓት ፕሮጀክት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው

ጥር 27/2014 (ዋልታ) የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሃብት ማሳወቂያና ምዝገባ ዲጂታል ሥርዓት ፕሮጀክት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የየክልል ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ዲጂታል የሃብት ምዝገባ ፕሮጀክቱ ሙስናን እንደምቀንስ ገልጸው የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስበት ከኢንሳ ጋር እንደሚሰራ እና የኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አተገባበሩ ላይ እንቅፋት እንዳይገጥመው እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በቀጣይ የአመራርና የተሿሚዎችን ሃብት በኤሌክትሮኒክስ ምዝገባ ለማካሄድና ለመቆጣጠር የዲጂታል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች ተሿሚዎች ላይ ተፈፃሚ ይሆናልም ነው የተባለው፡፡
ከኮሚሽኑ መረጃ የሚፈልጉ ሰዎች በአካል ሳይገኙ መረጃ ያገኛሉ የተባለ ሲሆን ቤተሰብን የሚመለከት የምዝገባ መረጃ ለፍትህ ካልተፈለገ በስተቀር በሚስጥር የሚያዝ ነውም ተብሏል።
ማንኛውም ሰው የሃብት ምዝገባ አዋጁን ጥሷል በሚለው ተሿሚ፣ ተመራጭ ወይም የተቋም ሰራተኛ ላይ ጥቆማ ማቅረብ ይችላል የተባለ ሲሆን ጥቆማ አቅራቢው 25 በመቶ ድርሻ እንደሚሰጠው ተጠቁሟል።
የሃብት ማሳወቅ ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ሥራ ከጀመረ 10ኛ ዓመቱን ይዟል።
ተስፋዬ አባተ