የህብረ ብሄራዊ አንድነታችን መገለጫ የሆነው ልዩነታችን ውበታችን ነው – ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

የኢፌዴሪ  ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

15ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አገር አቀፍ የሲምፖዚየም መርሃ-ግብር እየተካሄደ ነው።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሲምፖዚየሙን በይፋ ሲከፍቱ የህብረ ብሄራዊ አንድነታችን መገለጫ የሆነው ልዩነታችን ውበታችን ነው፤ ይህ ከየቦታው መጥቶ በአንድ ላይ እንደሚፈስ ወንዝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገራዊ አንድነት ማጠናከር ይገባቸዋልም ብለዋል።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ላለፉት አመታት ሀገሪቱን በእኩይ ተግባሩ ሲያምስና ሲንቀሳቀስ የነበረው የህወሓት ጁንታ ቡድን የተወገደበት በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው በመግለጽ ዋጋ ለከፈሉት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ክብር ይገባል ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለሚከፋፍላቸው እድል ሳይሰጡ ሕብረ ብሔራዊነት አንድነታቸዉን ማጠናከር እንዳለባቸው አስታውሰዋል።

ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በማክበርና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትትን በማረጋገጥ የጋራ እሴቶች ላይ መስራት እንደሚገባም አንስተዋል።

በሲምፖዝየሙ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች ፣ የሀገር ሽማየግሌዋች እና የሐይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል “እኩልነትና ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልፅግና” በሚል መርህ አዲስ አበባ፣ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ተከብሯል።

 

(በህይወት አክሊሉ)