የህወሃት ቡድን ለ27 አመታት በክልሉ ሲዘርፍ ኖረ እንጂ ልማት እንዲሰራ አለማድረጉ ተገለጸ

ሐምሌ 28/2013 (ዋልታ) – የህወሐት አሸባሪ ቡድን ለ27 አመታት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲዘርፍ  ኖረ እንጂ  እዚህ ግባ የሚባል ልማት እንዲከናወን አለማድረጉ ተገለጸ።

በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ ከ24 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነቡ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ህንጻ ተመርቋል።

በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሀይል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ፣ የህወሃት አሸባሪ ቡድን በ27 አመታት የስልጣን ዘመኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲዘርፍ ኖረ እንጂ ልማት እንዲከናወን አላደረገም ብለዋል።

በወረዳው የተከናወነው ግንባታ ለሌሎች ወረዳዎችም በአርአያነት የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር በተጓዳኝ የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በክልሉ የተለያዩ ሃብቶችን ከመዝረፍ ውጭ ልማት እንዲከናወን ሳያደርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በተለይም የመተከል ዞን ካለው የተፈጥሮ ሃብት አንጻር ብዙ ሊለማ የሚችል ቢሆንም ከመስራት ይልቅ አሸባሪ ቡድኑ ሲርፈው ኖሯል።

በ27 አመታት የአካባቢውን ሀብት ሲዘርፍ ቆይቶ የመንገድ ግንባታ እንኳን እንዲከናወን አላደረገም ነው ያሉት።

በመሆኑም በቀጣይ ህብረተሰቡ የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን ከማከናወን በተጓዳኝ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት ሌተናል ጀነራል አስራት።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጋሹ ዱጋዝ፤ በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መደረጉን  ገልጸዋል።

የዞኑን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ሃይል በጋራ እየሰሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም በጋራ ለሰላምና ልማት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎችም ልማታችንን እያከናወን፤ ሰላምና አብሮነታችንን ለማጠናከር በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

በአካባቢው ሰላም እንዲደፈርስ የሚሰሩ አካላትን መንግስት እየተከታተለ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።