የህወሓት የሽብር ቡድን ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት ነው – አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – የህወሓት የሽብር ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንትና አካባቢው፤ በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ፣ መርሳና አካባቢው፤ እንዲሁም በዋግህምራ ዞን ሰቆጣና አካባቢው እየተሰወደበት ባለው ወታደራዊ እርምጃ ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ገለፀ፡፡
የፅህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የሽብር ቡድኑ ትላልቅ አዋጊዎች መገደላቸውን እና በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎችም መማረካቸውን ገልፀዋል፡፡
የህወሓት የሽብር ቡድን በኃይል በወረራቸው አካባቢዎች ወጣቶች ታፍነው ተወስደዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ንብረቶችም ተዘርፈዋል ብለዋል፡፡
በዚህ ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ መሆኑን አቶ ግዛቸው ለኢብኮ አስታውቀዋል፡፡
የህወሓት የሽብር ቡድንን ለመደምሰስ የተላለፈውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ ህብረተሰቡ የሽብር ቡድኑን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን ያሳየው ተነሳሽነትና ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
አቶ ግዛቸው በአጠቃላይ ህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ተደራጅቶ አካባቢውን በንቃት መከታተል እና ከሽብር ቡድኑ ሰርጎ ገቦች መጠበቅ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የህልውና ዘመቻውን በገንዘብና አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡