የህዳር ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት የ20.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተባለ

በህዳር ወር 2013 ዓ.ም የተመዘገበው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ20 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በህዳር ወር 2013 ዓ.ም አገራዊ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የምግብ የዋጋ ግሽበት ደግሞ በ23 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ ምግብ ነክ ያልሆኑ ነገሮች የዋጋ ግሽበትም በ17 ነጥብ 1 በመቶ መጨመሩን ኤጀንሲው አስታውቋል።

የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ግሽበት ረዘም ያለ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ የሚያሳይ ነው፡፡

የህዳር ወር 2013 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ19 ነጥብ 0 ከመቶ ከፍ ብሏል፡፡

እየተጠናቀቀ ባለው የህዳር ወር የታየው የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ህዳር ወር 2012 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ22 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

በተያዘው የህዳር ወር አንዳንድ የእህል ዓይነቶች መጠነኛ ቅናሽ ያሳዩ ሲሆን፣ ይህም ለምግብ ዋጋ ግሽበት መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በአትክልትና በአንዳንድ የጥራጥሬ ዓይነቶች መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ ተመዝግቧል።

በሌላ በኩል ስኳር፣ ከውጭ የሚገባ የምግብ ዘይት፣ ድንች እና ቡና ዋጋ ጭማሪ በማሳየታቸው ለዋጋ ግሽበት ምጣኔ መጨመር አስተዋጽኦ አድርገዋል ብሏል ኤጀንሲው በመግለጫው።

ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ከአሁኑ ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በንጽጽር ሲታይ ዝቅተኛ ስለነበር የዋጋ ግሽበቱ ከፍ ብሎ ታይቷል ብሏል፡፡

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ባልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች በህዳር ወር 2013 ዓ.ም የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ህዳር ወር 2012 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸርም በ15 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ለዚህም በዋናነት ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል በተለይ በአልኮልና ትምባሆ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ በቤት መስሪያ እቃዎች፣ በህክምና መሳሪያዎች እና በጌጣጌጥ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ እንደሚጠቀሱ ኤጀንሲው ማሳወቁን ኢዜአ ዘግቧል።