ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ በዲፕሎማሲው መስክ የተሰራው ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ግብፅና ሱዳን የውሃ ሙሌቱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይከናወን ብዙ ርቀት መጓዛቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ጴጥሮስ፣ ተደራዳሪዎቻችን የሀገራቱን ተለዋዋጭና ተገማች ያልሆነ አደገኛ የድርድር ሂደት ቀድሞ መረዳትና በአግባቡ መመከት በመቻላቸው ዕቅዳቸው መክሸፉን ገልፀዋል።
የድርድር ሂደቱና የተገኘው ውጤት የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ዳግም ለአለም ያረጋገጠ እንደሆነና በተገኘው ዲፕሎማሲያዊ ድል መዘናጋት እንደማይገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ግብፅና ሱዳን በህዳሴው ግድባችን ላይ የሚያደርጉትን ትንኮሳ ይተዋሉ የሚል የግል እምነት እንደሌላቸው ጠቁመው፣ ግንባታው ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ በዲፕሎማሲውም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የሚገጥሙንን መሰናክሎች ለማለፍ ከወዲሁ ዝግጁ መሆን ይኖርብናል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳነት ዶ/ር ካሳሁን ወዳጆ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል።
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የግድቡን ስራ በተለያየ መንገድ ሲደግፍ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ሁለንተናዊ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አመራሩን እና አጠቃላይ የተቋሙን ማህበረሰብ በማስተባበር ለግድቡ ግንባታ በከፍተኛ ተነሳሽነት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ከለለው አዲሱ ተናግረዋል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት ብቻ አመራሩን ጨምሮ ሁሉም የተቋሙ ማህበረሰብ የ1 ወር ደመወዙን ለቦንድ ግዢ በማዋል በአጠቃላይ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ድጋፉ ግድቡ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እስኪጀምር ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናልም ብለዋል፡፡