የ“ሆሣዕና በአርያም” በዓል በኦርቶዶክስ ተዋኅዶ አማኞች ዘንድ ተከበረ

ሚያዝያ 9/2014 (ዋልታ) የ “ሆሣዕና በአርያም” በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ አማኞች ዘንድ ተከብሯል፡፡

ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ሲሆን ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።

ሆሣዕና ማለት የቃሉ ትርጉም በአርማይክ ቋንቋ አሁን አድን ማለት ሲሆን በግእዝ ደግሞ መድሀኒት ማለት ነው፡፡

የሆሣዕና በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የነቢያትን ትንቢት ለመፈጸም በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩስአሌም ሲገባ በፊት በኃላው በቀኝ በግራው በበርካታ ሕዝቦች እና አፍ ባልፈቱ ህጻናት ጭምር “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት፣ ሆሣዕና በአርያም” በማለት ኢየሱስ ክርስቶስን መቀበላቸው በክብር የሚታወስበት ታላቅ በዓል መሆኑን ቅድስት ቤተክርስቲያን ታስተምራለች።

ኢየሱስ ክርስቶስ የነቢያትን ትንቢት ለመፈጸም በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩስአሌም ሲገባ፤ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም” በማለት በክብር መቀበላቸውን እምነቱ ሲያስተምር ለዚህም ነው ይህ ቀን በየዓመቱ የሚታወሰው ይላሉ የሀይማኖቱ መምህር ሊቀ ማዕምራን ፅጌ ከበረ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በዝማሬና በእልልታ ታጅቦ ወደ እየሩሳሌም በገባበት ወቅት ጸሀፍት ፈሪሳውያንና ሊቀ ካህናቱ ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱን የሚናገሩት መምህሩ፤ በዚህ ወቅት ኢየሱስ በሰዎች ዘንድ ሊኖር የሚገባውን መከባበርና መቻቻልን ያስተማረበት አጋጣሚ ነበር ብለዋል፡፡

ለዚህም “እኛም የእምነቱ ተከታዮች ሌሎች ተረድተውንም ይሁን ሳይረዱን ለሚመጣብን ቁጣ ሰከን ባለ መንገድ ምላሽ መስጠት እንዳለብን ያስተምራል” ነው ያሉት፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ የመታየቱ ምስጢር ቅዱሳን ነብያት በዘመናቸው የነበሩትን አማኞች ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅርና የይቅርታ እንዲሁም የምህረት ዘመን ስለመሆኑ የሚያመላክቱበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረባቸው ጊዜያት የሰው ልጅ በፍቅር በይቅርታ በመከባበር እና በመተሳሰብ እንዲኖር አስተምሯል የሚሉት መምህሩ “እኛም ከእርሱ በቀሰምነው ትምህርት በፆም ወቅት በምናዳብረው ግብርና ከዚያም በኋላ ለሰው ልጅ ክብርን በመስጠት በመተሳሰብና በመከባበር መኖር ይገባናል” ብለዋል፡፡

ለዚህም የበደለን ይቅር ማለት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን አስታውሰዋል ሊቀ ማዕምራን ፅጌ ከበረ፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት